text
stringlengths
4
267
እንዲህም አሉ፦ “ያለህና የነበርክ፣ ሁሉን ቻይ የሆንከው ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ ታላቅ ኃይልህን ስለያዝክና ንጉሥ ሆነህ መግዛት ስለጀመርክ እናመሰግንሃለን።
ሆኖም ብሔራት ተቆጡ፤ የአንተም ቁጣ መጣ፤ በሙታን ላይ የምትፈርድበት፣ ለባሪያዎችህ ለነቢያት፣ ለቅዱሳንና ስምህን ለሚፈሩ ለታናናሾችና ለታላላቆች ወሮታ የምትከፍልበት እንዲሁም ምድርን እያጠፉ ያሉትን የምታጠፋበት የተወሰነው ጊዜ መጣ።”
በሰማይ ያለው የአምላክ ቤተ መቅደስ ቅዱስ ስፍራ ተከፍቶ ነበር፤ የቃል ኪዳኑ ታቦትም በቤተ መቅደሱ ቅዱስ ስፍራ ታየ። እንዲሁም የመብረቅ ብልጭታ፣ ድምፅ፣ ነጎድጓድ፣ የምድር ነውጥና ታላቅ በረዶ ተከሰተ።
በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ነገሮች ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ አምላክ ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውና እሱ የገለጠው ራእይ ይህ ነው። ኢየሱስም መልአኩን ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ በምልክቶች ገለጠለት፤
ዮሐንስም አምላክ ስለሰጠው ቃልና ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሰጠው ምሥክርነት ይኸውም ስላያቸው ነገሮች ሁሉ መሥክሯል።
የዚህን ትንቢት ቃል ጮክ ብሎ የሚያነብ ደስተኛ ነው፤ እንዲሁም ቃሉን የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፉትን ነገሮች የሚጠብቁት ደስተኞች ናቸው፤ የተወሰነው ጊዜ ቀርቧልና።
ከዮሐንስ፣ በእስያ አውራጃ ለሚገኙ ለሰባቱ ጉባኤዎች፦ “ካለው፣ ከነበረውና ከሚመጣው” እንዲሁም በዙፋኑ ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን፤
በተጨማሪም “ታማኝ ምሥክር፣” “ከሙታን በኩር” እና “የምድር ነገሥታት ገዢ” ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ለወደደንና በገዛ ደሙ አማካኝነት ከኃጢአታችን ነፃ ላወጣን፣
ነገሥታት እንዲሁም ለአምላኩና ለአባቱ ካህናት ላደረገን ለእሱ ክብርና ኃይል ለዘላለም ይሁን። አሜን።
እነሆ፣ ከደመናት ጋር ይመጣል፤ ዓይኖች ሁሉ፣ የወጉትም ያዩታል፤ በእሱም የተነሳ የምድር ነገዶች ሁሉ በሐዘን ደረታቸውን ይደቃሉ። አዎ፣ ይህ በእርግጥ ይሆናል። አሜን።
“እኔ አልፋና ኦሜጋ፣ ያለው፣ የነበረውና የሚመጣው፣ ሁሉን ቻይ ነኝ” ይላል ይሖዋ አምላክ።
የኢየሱስ ተከታይ በመሆኔ ከእናንተ ጋር የመከራው፣ የመንግሥቱና የጽናቱ ተካፋይ የሆንኩ እኔ ወንድማችሁ ዮሐንስ፣ ስለ አምላክ በመናገሬና ስለ ኢየሱስ በመመሥከሬ ጳጥሞስ በምትባል ደሴት ነበርኩ።
በመንፈስ ወደ ጌታ ቀን ተወሰድኩ፤ ከኋላዬም እንደ መለከት ያለ ኃይለኛ ድምፅ ሰማሁ፤
እንዲህም አለኝ፦ “የምታየውን በመጽሐፍ ጥቅልል ላይ ጽፈህ በኤፌሶን፣ በሰምርኔስ፣ በጴርጋሞን፣ በትያጥሮን፣ በሰርዴስ፣ በፊላደልፊያና በሎዶቅያ ለሚገኙት ለሰባቱ ጉባኤዎች ላከው።”
እኔም እያናገረኝ ያለው ማን እንደሆነ ለማየት ዞር አልኩ፤ በዚህ ጊዜም ሰባት የወርቅ መቅረዞች ተመለከትኩ፤
በመቅረዞቹም መካከል የሰው ልጅ የሚመስል አየሁ፤ እሱም እስከ እግሩ የሚደርስ ልብስ የለበሰና ደረቱ ላይ የወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ ነበር።
በተጨማሪም ራሱና ፀጉሩ እንደ ነጭ ሱፍ፣ እንደ በረዶም ነጭ ነበር፤ ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፤
እግሮቹም እቶን ውስጥ እንደጋለ የጠራ መዳብ ነበሩ፤ ድምፁም እንደ ውኃ ፏፏቴ ነበር።
በቀኝ እጁም ሰባት ከዋክብት ይዞ ነበር፤ ከአፉም በሁለቱም በኩል ስለት ያለው ረጅም ሰይፍ ወጣ፤ ፊቱም በሙሉ ድምቀቱ እንደሚያበራ ፀሐይ ነበር።
ባየሁት ጊዜ እንደሞተ ሰው ሆኜ እግሩ ሥር ወደቅኩ። እሱም ቀኝ እጁን በላዬ ጭኖ እንዲህ አለኝ፦ “አትፍራ። እኔ የመጀመሪያውና የመጨረሻው ነኝ፤
ሕያው የሆነውም እኔ ነኝ፤ ሞቼም ነበር፤ አሁን ግን ለዘላለም እኖራለሁ፤ የሞትና የመቃብር ቁልፎችም አሉኝ።
ስለዚህ ያየሃቸውን ነገሮች፣ አሁን እየተከናወኑ ያሉትንና ከእነዚህ በኋላ የሚፈጸሙትን ነገሮች ጻፍ።
በቀኝ እጄ ላይ ያየሃቸው የሰባቱ ከዋክብት እንዲሁም የሰባቱ የወርቅ መቅረዞች ቅዱስ ሚስጥር ይህ ነው፦ ሰባቱ ከዋክብት የሰባቱን ጉባኤዎች መላእክት ያመለክታሉ፤ ሰባቱ መቅረዞች ደግሞ ሰባቱን ጉባኤዎች ያመለክታሉ።
ከዚህ በኋላ አራት መላእክት በአራቱ የምድር ማዕዘናት ቆመው አየሁ፤ እነሱም በምድር ወይም በባሕር ወይም በማንኛውም ዛፍ ላይ ምንም ነፋስ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሳት አጥብቀው ይዘው ነበር።
እንዲሁም የሕያው አምላክ ማኅተም ያለው ሌላ መልአክ ከፀሐይ መውጫ ወደ ላይ ሲወጣ አየሁ፤ እሱም ምድርንና ባሕርን እንዲጎዱ ሥልጣን የተሰጣቸውን አራቱን መላእክት በታላቅ ድምፅ
እንዲህ አላቸው፦ “የአምላካችንን ባሪያዎች ግንባራቸው ላይ ማኅተም እስክናደርግባቸው ድረስ ምድርን ወይም ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጉዱ።”
የታተሙትን ሰዎች ቁጥር ሰማሁ፤ ቁጥራቸው 144,000 ሲሆን የታተሙትም ከእያንዳንዱ የእስራኤል ልጆች ነገድ ነበር፦
ከይሁዳ ነገድ 12,000 ታተሙ፤ከሮቤል ነገድ 12,000፣ከጋድ ነገድ 12,000፣
ከአሴር ነገድ 12,000፣ከንፍታሌም ነገድ 12,000፣ከምናሴ ነገድ 12,000፣
ከስምዖን ነገድ 12,000፣ከሌዊ ነገድ 12,000፣ከይሳኮር ነገድ 12,000፣
ከዛብሎን ነገድ 12,000፣ከዮሴፍ ነገድ 12,000፣ከቢንያም ነገድ 12,000 ታተሙ።
ከዚህ በኋላ አየሁ፤ እነሆም፣ ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ አንድም ሰው ሊቆጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ሕዝብ ነጭ ልብስ ለብሰው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆመው ነበር፤ የዘንባባ ዝንጣፊዎችንም በእጆቻቸው ይዘው ነበር።
በታላቅም ድምፅ እየጮኹ “መዳን ያገኘነው በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ከአምላካችን እንዲሁም ከበጉ ነው” ይሉ ነበር።
መላእክቱ ሁሉ በዙፋኑ፣ በሽማግሌዎቹና በአራቱ ሕያዋን ፍጥረታት ዙሪያ ቆመው ነበር፤ እነሱም በዙፋኑ ፊት በግንባራቸው ተደፍተው ለአምላክ ሰገዱ፤
እንዲህም አሉ፦ “አሜን! ውዳሴ፣ ግርማ፣ ጥበብ፣ ምስጋና፣ ክብር፣ ኃይልና ብርታት ለዘላለም ለአምላካችን ይሁን። አሜን።”
ከሽማግሌዎቹ አንዱ መልሶ “እነዚህ ነጭ ልብስ የለበሱት እነማን ናቸው? ከወዴትስ የመጡ ናቸው?” አለኝ።
እኔም ወዲያውኑ “ጌታዬ፣ የምታውቀው አንተ ነህ” አልኩት። እሱም እንዲህ አለኝ፦ “እነዚህ ታላቁን መከራ አልፈው የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው ነጭ አድርገውታል።
በአምላክ ዙፋን ፊት ያሉትም ለዚህ ነው፤ በቤተ መቅደሱም ቀንና ሌሊት ቅዱስ አገልግሎት እያቀረቡለት ነው፤ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም ድንኳኑን በላያቸው ይዘረጋል።
ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም እንዲሁም አይጠሙም፤ ፀሐይ አይመታቸውም፤ ሐሩሩም አያቃጥላቸውም፤
ምክንያቱም በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናል፤ ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭም ይመራቸዋል። አምላክም እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል።”
እሱም በባሕር አሸዋ ላይ ቆመ። እኔም አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ያሉት አንድ አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ በቀንዶቹም ላይ አሥር ዘውዶች የነበሩት ሲሆን በራሶቹ ላይ አምላክን የሚሰድቡ ስሞች ነበሩት።
ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፤ እግሮቹ ግን የድብ እግር፣ አፉ ደግሞ የአንበሳ አፍ ይመስል ነበር። ዘንዶውምለአውሬው ኃይልና ዙፋን እንዲሁም ታላቅ ሥልጣን ሰጠው።
እኔም አየሁ፤ ከአውሬው ራሶች አንዱ የሞተ ያህል እስኪሆን ድረስ ቆስሎ ነበር፤ ሆኖም ለሞት የሚዳርገው ቁስሉ ዳነ፤ ምድርም ሁሉ አውሬውን በአድናቆት ተከተለው።
ሰዎችም ዘንዶው ለአውሬው ሥልጣን ስለሰጠው ዘንዶውን አመለኩ፤ እንዲሁም “እንደ አውሬው ያለ ማን ነው? ከእሱስ ጋር ማን ሊዋጋ ይችላል?” በማለት አውሬውን አመለኩ።
እሱም የትዕቢት ቃል የሚናገርበትና አምላክን የሚሳደብበት አፍ ተሰጠው፤ ደግሞም ለ42 ወር የፈለገውን እንዲያደርግ ሥልጣን ተሰጠው።
አምላክን ለመሳደብ ይኸውም የአምላክን ስምና የአምላክን መኖሪያ እንዲሁም በሰማይ የሚኖሩትን ለመሳደብ አፉን ከፈተ።
ቅዱሳኑን እንዲዋጋና ድል እንዲያደርጋቸው ተፈቀደለት፤ ደግሞም በነገድ፣ በሕዝብ፣ በቋንቋና በብሔር ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው።
በምድር ላይ የሚኖሩም ሁሉ ያመልኩታል። ዓለም ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የአንዳቸውም ስም በታረደው በግ የሕይወት መጽሐፍ ጥቅልል ላይ አልሰፈረም።
ጆሮ ያለው ካለ ይስማ።
ማንም ሰው መማረክ ካለበት ይማረካል። በሰይፍ የሚገድል ካለ በሰይፍ መገደል አለበት። ቅዱሳን ጽናትና እምነት ማሳየት የሚያስፈልጋቸው እዚህ ላይ ነው።
ከዚያም ሌላ አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፤ እሱም እንደ በግ ሁለት ቀንዶች ነበሩት፤ ሆኖም እንደ ዘንዶ መናገር ጀመረ።
በመጀመሪያው አውሬ ፊት የመጀመሪያውን አውሬ ሥልጣን ሙሉ በሙሉ ይጠቀማል። ምድርና የምድር ነዋሪዎች፣ ለሞት የሚዳርገው ቁስል የዳነለትን የመጀመሪያውን አውሬ እንዲያመልኩ ያደርጋል።
በሰው ልጆችም ፊት ታላላቅ ምልክቶችን ይፈጽማል፤ እሳትንም እንኳ ከሰማይ ወደ ምድር ያወርዳል።
በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች በሰይፍ ቆስሎ ለነበረው በኋላ ግን ላገገመው አውሬ፣ ምስል እንዲሠሩ እያዘዘ በአውሬው ፊት እንዲፈጽማቸው በተፈቀዱለት ምልክቶች አማካኝነት በምድር ላይ የሚኖሩትን ያስታል።
እንዲሁም ለአውሬው ምስል እስትንፋስ እንዲሰጠው ተፈቀደለት፤ ይህም የሆነው የአውሬው ምስል መናገር እንዲችልና የአውሬውን ምስል የማያመልኩትን ሁሉ እንዲያስገድል ነው።
ሰዎች ሁሉ ማለትም ታናናሾችና ታላላቆች፣ ሀብታሞችና ድሆች እንዲሁም ነፃ ሰዎችና ባሪያዎች በቀኝ እጃቸው ወይም በግንባራቸው ላይ ምልክት እንዲደረግባቸው አስገደደ፤
ይህም የሆነው ምልክቱ ይኸውም የአውሬው ስም ወይም የስሙ ቁጥር ካለው ሰው በስተቀር ማንም መግዛት ወይም መሸጥ እንዳይችል ነው።
ጥበብ የሚያስፈልገው እዚህ ላይ ነው፦ የማስተዋል ችሎታ ያለው ሰው የአውሬውን ቁጥር ያስላ፤ ቁጥሩ የሰው ቁጥር ነውና፤ ቁጥሩም 666 ነው።
እኔም አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ፤ የቀድሞው ሰማይና የቀድሞው ምድር አልፈዋልና፤ ባሕሩም ከእንግዲህ ወዲህ የለም።
ደግሞም ቅድስቲቱ ከተማ፣ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ከሰማይ ከአምላክ ዘንድ ስትወርድ አየሁ፤ እሷም ለባሏ እንዳጌጠች ሙሽራ ተዘጋጅታ ነበር።
በዚህ ጊዜ ከዙፋኑ አንድ ታላቅ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፦ “እነሆ፣ የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ እሱም ከእነሱ ጋር ይኖራል፤ እነሱም ሕዝቡ ይሆናሉ። አምላክ ራሱም ከእነሱ ጋር ይሆናል።
እሱም እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”
በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው “እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ” አለ። ደግሞም “እነዚህ ቃላት አስተማማኝና እውነት ስለሆኑ ጻፍ” አለኝ።
እንዲህም አለኝ፦ “እነዚህ ነገሮች ተፈጽመዋል! እኔ አልፋና ኦሜጋ፣ የመጀመሪያውና የመጨረሻው ነኝ። ለተጠማ ሁሉ ከሕይወት ውኃ ምንጭ በነፃ እሰጣለሁ።
ድል የሚነሳ ሁሉ እነዚህን ነገሮች ይወርሳል፤ እኔ አምላክ እሆነዋለሁ፤ እሱም ልጄ ይሆናል።
ይሁን እንጂ የፈሪዎች፣ የእምነት የለሾች፣ ርኩስና አስጸያፊ የሆኑ ሰዎች፣ የነፍሰ ገዳዮች፣ የሴሰኞች፣ መናፍስታዊ ድርጊት የሚፈጽሙ፣ የጣዖት አምላኪዎችና የውሸታሞች ሁሉ ዕጣ ፋንታቸው በእሳትና በድኝ በሚቃጠል ሐይቅ ውስጥ መጣል ነው። ይህ ሁለተኛውን ሞት ያመለክታል።”
በሰባቱ የመጨረሻ መቅሰፍቶች የተሞሉትን ሰባቱን ሳህኖች ይዘው ከነበሩት ሰባት መላእክት አንዱ መጥቶ “ና፣ የበጉን ሚስት፣ ሙሽራይቱን አሳይሃለሁ” አለኝ።
ከዚያም በመንፈስ ኃይል ወደ አንድ ትልቅና ረጅም ተራራ ወሰደኝና ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ከሰማይ ከአምላክ ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ፤
እሷም የአምላክን ክብር ተላብሳ ነበር። የብርሃኗም ድምቀት እጅግ እንደከበረ ድንጋይ ይኸውም እንደ ኢያስጲድ ነበር፤ ደግሞም እንደ ክሪስታል ጥርት ብሎ ያንጸባርቅ ነበር።
ትልቅና ረጅም የግንብ አጥር እንዲሁም 12 በሮች ነበሯት፤ በበሮቹም ላይ 12 መላእክት ነበሩ፤ የ12ቱም የእስራኤል ልጆች ነገዶች ስም በበሮቹ ላይ ተቀርጾ ነበር።
በምሥራቅ ሦስት በሮች፣ በሰሜን ሦስት በሮች፣ በደቡብ ሦስት በሮችና በምዕራብ ሦስት በሮች ነበሩ።
በተጨማሪም የከተማዋ የግንብ አጥር 12 የመሠረት ድንጋዮች ነበሩት፤ በእነሱም ላይ የ12ቱ የበጉ ሐዋርያት 12 ስሞች ተጽፈው ነበር።
እያነጋገረኝ የነበረው መልአክም ከተማዋን፣ በሮቿንና የግንብ አጥሯን ለመለካት የሚያገለግል የወርቅ ዘንግ ይዞ ነበር።
ከተማዋ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያላት ሲሆን ርዝመቷ ከወርዷ ጋር እኩል ነው። እሱም ከተማዋን በዘንጉ ሲለካት 2,220 ኪሎ ሜትር ገደማ ሆና ተገኘች፤ ርዝመቷ፣ ወርዷና ከፍታዋ እኩል ነው።
በተጨማሪም የግንብ አጥሯን ለካ፤ አጥሩም በሰው መለኪያ፣ በመልአክም መለኪያ 144 ክንድ ሆኖ ተገኘ።
የከተማዋ የግንብ አጥር የተገነባው ከኢያስጲድ ነበር፤ ከተማዋም የጠራ መስተዋት የሚመስል ንጹሕ ወርቅ ነበረች።
የከተማዋ የግንብ አጥር መሠረቶች በተለያዩ የከበሩ ድንጋዮች ያጌጡ ነበሩ፦ የመጀመሪያው መሠረት ኢያስጲድ፣ ሁለተኛው ሰንፔር፣ ሦስተኛው ኬልቄዶን፣ አራተኛው መረግድ፣
አምስተኛው ሰርዶንክስ፣ ስድስተኛው ሰርድዮን፣ ሰባተኛው ክርስቲሎቤ፣ ስምንተኛው ቢረሌ፣ ዘጠነኛው ቶጳዝዮን፣ አሥረኛው ክርስጵራስስ፣ አሥራ አንደኛው ያክንትና አሥራ ሁለተኛው አሜቴስጢኖስ ነበር።
በተጨማሪም 12ቱ በሮች 12 ዕንቁዎች ነበሩ፤ እያንዳንዱ በር ከአንድ ዕንቁ የተሠራ ነበር። የከተማዋ አውራ ጎዳናም ብርሃን እንደሚያስተላልፍ መስተዋት ንጹሕ ወርቅ ነበር።
በከተማዋ ውስጥ ቤተ መቅደስ አላየሁም፤ ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ አምላክና በጉ ቤተ መቅደሷ ናቸውና።
ከተማዋ የፀሐይም ሆነ የጨረቃ ብርሃን አላስፈለጋትም፤ የአምላክ ክብር ብርሃን ሰጥቷታልና፤ በጉም መብራቷ ነበር።
ብሔራትም በእሷ ብርሃን ይጓዛሉ፤ የምድር ነገሥታትም ክብራቸውን ወደ እሷ ያመጣሉ።
በሮቿ በቀን አይዘጉም፤ በዚያም ሌሊት ፈጽሞ አይኖርም።
የብሔራትን ግርማና ክብርም ወደ እሷ ያመጣሉ።
ሆኖም የረከሰ ማንኛውም ነገር እንዲሁም አስጸያፊ ነገር የሚያደርግና የሚያታልል ማንኛውም ሰው በምንም ዓይነት ወደ እሷ አይገባም፤ ወደ እሷ የሚገቡት በበጉ የሕይወት መጽሐፍ ጥቅልል ላይ የተጻፉ ብቻ ናቸው።
“በሰርዴስ ላለው ጉባኤ መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ ሰባቱ የአምላክ መናፍስት ያሉትና ሰባቱን ከዋክብት የያዘው እንዲህ ይላል፦ ‘ሥራህን አውቃለሁ፤ ሕያው ነው የሚል ስም አለህ፤ ነገር ግን ሞተሃል።
ሥራህን በአምላኬ ፊት በተሟላ ሁኔታ ተጠናቆ ስላላገኘሁት ንቃ፤ ሊሞቱ የተቃረቡትን የቀሩትን ነገሮችም አጠናክር።
ስለዚህ የተቀበልከውንና የሰማኸውን ምንጊዜም አስብ፤ እንዲሁም ዘወትር ጠብቀው፤ ንስሐም ግባ። ካልነቃህ ግን እንደ ሌባ እመጣለሁ፤ በየትኛው ሰዓት ከተፍ እንደምልብህም ፈጽሞ አታውቅም።
“‘ይሁን እንጂ ልብሳቸውን ያላረከሱ ጥቂት ሰዎች ከአንተ ጋር በሰርዴስ አሉ፤ እነሱም የሚገባቸው ስለሆኑ ነጭ ልብስ ለብሰው ከእኔ ጋር ይሄዳሉ።
ድል የሚነሳምልክ እንዲሁ ነጭ ልብስ ይለብሳል፤ እኔም ስሙን ከሕይወት መጽሐፍ በምንም ዓይነት አልደመስስም፤ ከዚህ ይልቅ በአባቴ ፊትና በመላእክቱ ፊት ለስሙ እመሠክራለሁ።
መንፈስ ለጉባኤዎቹ የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።’
“በፊላደልፊያ ላለው ጉባኤ መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ ቅዱስና እውነተኛ የሆነው፣ የዳዊት ቁልፍ ያለው፣ ማንም እንዳይዘጋ፣ የሚከፍተው እንዲሁም ማንም እንዳይከፍት፣ የሚዘጋው እሱ እንዲህ ይላል፦
‘ሥራህን አውቃለሁ፤ እነሆ፣ ማንም ሊዘጋው የማይችል የተከፈተ በር በፊትህ አድርጌአለሁ። ደግሞም ጥቂት ኃይል እንዳለህ አውቃለሁ፤ ቃሌንም ጠብቀሃል፤ ስሜንም አልካድክም።
እነሆ፣ አይሁዳውያን ሳይሆኑ አይሁዳውያን ነን እያሉ የሚዋሹት፣ ከሰይጣን ምኩራብ የሆኑት ወደ አንተ መጥተው በእግርህ ፊት እንዲሰግዱ አደርጋለሁ፤ እንዲሁም እንደወደድኩህ እንዲያውቁ አደርጋለሁ።
ስለ ጽናቴ የተነገረውን ቃል ስለጠበቅክ እኔም በምድር ላይ የሚኖሩትን ለመፈተን በመላው ምድር ላይ ከሚመጣው የፈተና ሰዓት እጠብቅሃለሁ።
ቶሎ እመጣለሁ። ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን ምንጊዜም አጥብቀህ ያዝ።
“‘ድል የሚነሳውን በአምላኬ ቤተ መቅደስ ዓምድ አደርገዋለሁ፤ ከዚያ በኋላም በምንም ዓይነት ከዚያ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን የአምላኬን ከተማ የአዲሲቱን ኢየሩሳሌም ስም እንዲሁም የእኔን አዲስ ስም በእሱ ላይ እጽፋለሁ።
መንፈስ ለጉባኤዎቹ የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።’
“በሎዶቅያ ላለው ጉባኤ መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ አሜን የሆነው፣ ታማኝና እውነተኛ ምሥክር እንዲሁም ከአምላክ ፍጥረት የመጀመሪያ የሆነው እንዲህ ይላል፦
‘ሥራህን አውቃለሁ፤ ወይ ቀዝቃዛ ወይ ትኩስ አይደለህም። ቀዝቃዛ ወይም ደግሞ ትኩስ ብትሆን ደስ ባለኝ ነበር።